ሙዳ(ብክነት)

ብክነቶችና የማስወገጃ ዘዴዎቻቸው

ካይዘን አንድ ተቋም የምርትና የአገልግሎት ጥራትን ዘወትር የማሻሻል ግቡን በመምታትና ደንበኞቹን ብሎም ተጠቃሚውን ለማርካት የሚያስችለውን ተቋማዊ የአሠራር ጠባዩንእና ሂደቱን የሚያሻሽልበት ዘለቄታዊ የአተገባበር አመራር ነው::ካይዘን በአንድ ተቋም ሲተገበር ዘላቂ፣ፈጣንእና ራስ-መርየአፈጻጸም ተመክሮ የሚኖረው ሲሆን ተልዕኮውን ማብቂያ በሌለው ለውጥ፣ጥራትና ምርታማነት ላይ ያደርጋል፡፡

በሥራ ሂደት ውስጥ የሚከሰት ማንኛውም ብክነት በጃፓንኛ ሙዳ ይባላል፡፡የካይዘን መሰረታዊ የአሰራር ዘዴ ሙሉ በሙሉ ብክነትን( Muda) የማስወገድ ስልት ይከተላል፡፡በአንድ ኢኮኖሚ ውስጥ ቁሳዊ ሀብት ለማምረት የዋለ ሥራ ምርታዊ ሥራ (Productive Labour) ይባላል፡፡

ብክነት ማለት በማንኛውም ምርታዊ ሥራ ውስጥ ፋይዳ የሌላቸው ፣ለምንሰጠው አገልግሎት ወይም ለምናመርተው ምርትምንም ዓይነት የጥራትም ሆነ የብዛት ለውጥ የማያመጡ፣የስራሂደታችንን አንቀው የሚይዙ፣በምርታዊ ሥራችን ላይም ወጪ የሚጨምሩ አላስፈላጊ ነገሮችን ያጠቃልላል፡፡ በአጠቃላይ ብክነት በምርታዊ ስራ ሂደት ውስጥ የማያስፈልጉ ወይንም እሴት የማይጨምሩ አሠራሮች ሲሆኑ ቶሎ መወገድ ያለባቸው አሠራሮች ናቸው፡፡
ከካይዘን ቀላል ቴክኒኮችና አፈጻጸሞች እንዲሁም መሠረታዊ የአሰራርዘዴዎች ውስጥ ሰባት የብክነት ዓይነቶች ያሉ ሲሆን በተጨማሪ ሙሪ እና ሙራ የሚባሉ የብክነት ዓይነቶች አሉ፡፡ስለሆነም የብክነት መንስኤዎች፣ብክነት የሚያስከትላቸው ችግሮች እንዲሁም መፍትሄዎችን የሚመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አጠናቅረናል፡፡

ሙሪ

ሙሪ የሚለው ቃል ጃፓንኛ ሲሆን ሰውን ጨምሮ እንስሳትንም ሆነ ማሽኖችን ከአቅም በላይ ማሰራት ፣ማስጨነቅ፣ወዘተ ነው፡፡ማንኛውም አምራች ሀይል የማምረትና የመንቀሳቀስ አቅሙ ውስን ነው፡፡ከአቅሙ በላይ እንዲንቀሳቀስ ካደረግነው ህይወት ያለው አምራች ለበሽታና ለሞት፤ ቁስ አካሉ ደግሞ ለብልሽት ይዳረጋል፡፡ከሁሉም በላይ ሰው ምትክ የሌለው ክቡር ፍጡር በመሆኑ በጥንቃቄና በክብር ሊያዝ ይገባል፡፡
ሙሪ የሚፈጠርባቸው በርካታ መንስኤዎች ቢኖሩም የሥራ ጫና እና የሰራተኛ አለመመጣጠን ፣ለስራው የተመደበው በጀት አነስተኛ መሆን ፣ለሰራተኞች(አንቀሳቃሾች) የማይመች አቋቋም(አቀማመጥ) ፣ጠንካራ የሥራ ቦታ ደህንነት አለመኖር ፣ጥራታቸውን የጠበቁ መለዋወጫዎች አለመኖር፣ የአቅርቦት እጥረት እና መጓተት ፣ የንድፍ ወይም የዲዛይን ግድፈቶች ይጠቀሳሉ፡፡
በታዳጊ አገሮች የሚገኙ ማምረቻዎች ጥራትን በሚፈለገው ደረጃ ለማሻሻል የካፒታልና የቴክኖሎጂ አቅማቸው ዝቅተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የተሟላ አሰራርና አደረጃጀት በመፍጠር ጥራቱ የተሟላ ምርት ማምረት ወጪን ይቀንሳል እንጂ አያበዛም፡፡ይልቁንም ወጪ የሚበዛው በሙሪ የተነሳ በየጊዜው የማሽኖች ብልሽት እየተፈጠረ ለጥገና ወጪ ሲወጣ ነው፡፡
ከዚህ አንጻር ምርትን ለመጨመር እና ትርፋማ ለመሆን በሚል የተሳሳተ አመለካከት በሰውም ሆነ በማሽን ላይ ጫና መፍጠር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡

ሙራ

ሙራ እንደሙሪ ከጃፓንኛ የተወሰደ ቃል ሲሆን ትርጉሙም በሰውም ሆነ በማሽን ላይ ያልተመጣጠነ የስራ ክፍፍል ማድረግ ነው፡፡ባልተመጣጠነ የስራ ከፍፍል ፤ ባልተመጣጠነ የማሽን አቅምና የተለያየ የግብዓት አቅርቦት እንዲሁም ወጥ ባልሆነ የሥራ መጠን ክፍፍል ይፈጠራል፡፡በቂ ያልሆነ ሥልጠና ወይም የመለዋወጫዎች ወጥ አለመሆን፣ የግብአቶች ጥራት መጓደል፣በእያንዳንዱ ማሽን ወጥ የሆነ(የተደላደለ) ምርት አለመኖር እና አላስፈሊጊ እንቅስቃሴ ወይም የመገልገያ እቃዎች አጠቃቀም ሙራ እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡

Designed by: HR ICT Solutions PLC  © Ethiopian Kaizen Institute