ትምህርታዊ ጽሁፍ

በካይዘን መሠረታዊ የአሰራር ዘዴ ውስጥ ሰባት አይነት ብክነቶች አሉ

1.ከሚያስፈልገው በላይ ማምረት

ምርት በጊዜ፣ በአይነት፣ በመጠን እና በይዘት ተጠቃሚዎች ወይም ደንበኞች ከሚፈልጉት በላይ ሲመረት የሚፈጠር የብክነት ዓይነት ነው፡፡ ለዚህ ዓይነት ብክነት መፈጠር መንስኤዎቹ በምርታዊ ሥራ ሂደት ውስጥ የሰው ኃይልና የማሽኖች የማምረት አቅም አለመመጣጠን፣ የሰራተኛ ሀብትና ማሽኖች ከሚፈለገው በላይ መብዛት፣ ብቃትና ጥራት ባለው የገበያ አመራር (marketing management) )አለመመራት ናቸው፡፡ በተጨማሪ በገፍ ማምረት ፣ምርትን በላይ በላዩ ማምረት ዘዴ እና ያልተደላደለ የአመራረት ዘዴ ይጠቀሳሉ፡፡ ገበያተኛን የማወቅ፣የማግኘት.፣የማበራከትና ቋሚ የማድረግ ጥረት ምርትን ወይም አገልግሎትን ለማዘጋጀት ከሚደረግ ጥረት ያላነሰ ትኩረት ይጠይቃል፡፡

የገበያ አመራር (marketing management)፣ የገበያ ፍላጎት (Demand)እንዲሁም አሁን ያሉ ድርጅቶች የማቅረብ ችሎታ (Supply)ምን ያህል እንደሆነ ማጥናትን ይጠይቃል፡፡ ከሚፈለገው በላይ ማምረት (“Muda” of Overproduction) የሚያስከትላቸው በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ረጅም የማስረከቢያ ጊዜን የማራዘም ፣ ለንብረት ቁጥጥር በቂ የግንዛቤ እጥረት እና ዝግጁ አለመሆን ፣ የቦታ ብክነት፣ የማጓጓዝ እና የፍተሻ ሥራዎች መብዛት፣ ቀጣይ የለውጥ ስራዎችን ማዳከም ፣ የካፒታል መባከን (መያዝ)እንዲሁም ለሥራ ማስኬጃ የሚያስፈልገንን የካፒታል መጠን መናርን ያስከትላል፡፡

ብክነቶችና የማስወገጃ ዘዴዎቻቸው ክፍል ሁለት

ባለፈው ክፍል አንድ ዕትማችን ሙሪና ሙራ የሚባሉ ቃላትን ፅንሰ ሃሳብ ገልጸን፤ ብክነት(Muda) የሚለው ደግሞ ምን እንደሆነ ለማብራራት ጀምረን ነበር ያቆምን፤የዛሬው ክፍል ሁለት ዝግጅትም ከዚያው የቀጠለ ነው፡፡መልካም ንባብ!

2.የንብረት ክምችት ብክነት

ለምርታዊ ስራ የሚያስፈልጉ በመጋዘን ውስጥ የሚቀመጡ ጥሬ እቃዎች፣መለዋወጫዎች ፣ምርቶች፣ተሰርተው ወይም ተገዝተው በመጋዘኖች ወይም በመደብሮች ውስጥ በሚኖሩ በርካታ ዕቃዎች የሚፈጠር መጠን የንብረት ክምችት ብክነት ይባላል፡፡በምርት ሂደት ውስጥ ላይ ያለ እቃም በሂሳብ አያያዝ እንደንብረት ክምችት ይቆጠራል፡፡

ያለበቂ ጥናት እና እውቀትን መሰረት ባላደረገ ትንበያ ማምረት፣ በስራ ክፍሎች መካከል ባለመናበብ ማምረት፣ ብዙ ክምችት መያዝ የሚያመጣቸውን ችግሮች አለመገንዘብ እንዲሁም ስርዓት የሌለው አቀማመጥ (Lay out) ፣ ወደፊት የምርት እጥረት ያጋጥማል በሚል እምነት በብዛት ማምረት፣ ወዘተ ለክምችት ብክነት መፈጠር በአቢይ መንስኤነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የንብረት ክምችት ብክነት አንድን ድርጅት ወደኪሳራ ሊወስደው ይችላል፡፡ምርት ከሚፈለገው በላይ ሲከማች ገንዘብ ስለሚይዝ አገላብጦ ሊሰራበት አይችልም፡፡በክምችት ላይ ያለው ምርት ቦታ ይይዛል፡፡የምርቱ መጠቀሚያ ጊዜ የሚያልፍ ከመሆኑ በላይ ሊበላሽ ይችላል፡፡በተጨማሪ የማሽኖችንና የሰዎችን አቅም ለመገመት ያዳግታል፡፡የንብረት ቁጥጥር ለማድረግ ጊዜ ከመውሰዱም በላይ የማምረት ሂደቱ ቀልጣፋ እንዳይሆን ያደርጋል፡፡

የንብረት ክምችት ብክነትን ለማስወገድ የተደላደለ (የተመቻቸ)፣ወጥ የሆነና በደንበኛው ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ምርታማነት እንዲኖር ማድረግ እና ፈጣንና ቀልጣፋ የክምችት ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ስለሆነም በተቻለ መጠን የክምችት መጠን በገበያ አመራር (marketing management) ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት፡፡ የምርት ክምችት መጠንም በደንበኞች ፍሰት ላይ የተመሰረተ ሆኖ ደንበኞች ሲመጡ ምርት ሁልጊዜ በእጃችን መኖር ያለበት መሆኑን የካይዘን ተመክሮ ያመለክታል፡፡

3.የመጠበቅ ብክነት

ይህ ብክነት በማምረት ሂደት በቅብብሎሽ ሰንሰለት ውስጥ በመዘግየት የሚከሰት ብክነትን የሚመለከት ሲሆን ጥሬ ዕቃን፣ አሰራርን(ኦፕሬሽን)፣ የማጓጓዝን እና ፍተሻን የመጠበቅና ቅድሚያ መስጠትን ያጠቃልላል፡፡

የመጠበቅ ብክነት(“Muda” of Waiting) መንስኤዎች በማምረት ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ ማነቆዎች ሲሆኑ በምርት መሳሪያዎች፣ በጥሬ ዕቃዎች፣በአሠራር ዘዴዎችና በሰው ኃይል ድክመቶች የሚከሰቱ እንዲሁም ጥራትና ብቃት ባለው ሁኔታ የሚሰራ የማሽኖች አተካከል (Lay out)፣ የአቅም አለመመጣጠን፣ የግብአቶችና ሌሎች የጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት፣ የባለድርሻ አካላት የጠበቀ ቅንጅት እና ትስስር አለመኖር፣ የባለሙያዎች አቅም ውስንነትና በሌሎችም ምክንያቶች ይፈጠራሉ፡፡
የመጠበቅ ብክነት አንድን ካምፓኒ ለኪሳራ ሊዳርግ የሚችል በመሆኑ ብክነቱ እንዳጋጠመ ቀጠሮ ሳይሰጥ በአሰቸኳይ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል፡፡

4. የማጓጓዝ ብክነት (Muda of Transportation)

ይህ የብክነት ዓይነት የሚፈጠረው በምርት ሥራ ሂደት ውስጥ ግብዓቶችንና ምርቶችን ወጪ፣ጊዜና እሴት ቆጣቢ ባልሆነ መንገድ በሚካሄድ ማጓጓዝ ነው፡፡ግብዓቶችንና ምርቶችን ለማጓጓዝ ቀልጣፋና ዘመናዊ የማጓጓዣ ዘዴዎችን መጠቀም በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ይሁን እንጂ ግብአቶችንና ምርቶችን እሴት በማይጨምር (Non-value added) መንገድ ካጓጓዝን ጊዜን፣ጉልበትን፣ገንዘብን እና ሌሎች እሴቶችን ማባከናችን አይቀርም፡፡

የማጓጓዝ ብክነት የሚያጋጥመው ዘመናዊ የሆኑ የመጓጓዣ ዘዴዎችን እንዲሁም ከማምረቻው ጋር ግንኙነት ያላቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እና ማሽኖችን ካለመጠቀም ነው፡፡በተጨማሪም ይህ ብክነት የሚያስከትለውን ጉዳት ካለመገንዘብ እንዲሁም የማምረቻ ቦታዎችን የቦታ አቀማመጥ፣ ምርቶችንና ግብአቶችን ቀልጣፋና ለስራ አመች በሆነ ዘዴ ካለማደራጀት ይከሰታል፡፡

በቂ ጥናት ባልተካሄደበት ምርታማነት ላይ የማጓጓዝ ብክነት (Muda of Transportation) ሊያጋጥም ይችላል፡፡በምርታማነት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በዚህ በኩል የማጓጓዝ ብክነት (Muda of Transportation) የሚያስከትላቸው ችግሮች በርካታ ቢሆኑም ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
ጊዜን፣ጉልበትን፣ገንዘብን እና ሌሎች እሴቶችን ማባከኑ፣ ዝቅተኛ የሆነ የሥራ ፍሰት መፍጠሩ፣ በማሽኖች ላይ ብክነትና ጉዳት እንዲያጋጥም ማድረጉ፣ የቦታ ብክነት እንዲከሰት ማድረጉ፣ ምርታማነት እንዲቀንስ ማድረጉ፣ በምርቶች ላይ ጉዳት ማጋጠሙ እና የማምረቻ ጊዜን ማራዘሙ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

5. ብልሽት (እንከን) ያለው ምርት የማምረት ብክነት

ብልሽት ወይም እንከን ያለው የማምረት ብክነት የሚፈጠረው በማምረት ሂደት ውስጥ ከሚመረቱት ምርቶች ውስጥ የጥራት ደረጃቸውን ሳያሟሉ በሚመረቱ ምርቶች ላይ ነው፡፡ይህም የሚከሰተው በምርት ሂደት ውስጥ ያልተሟላ የጥራት ፍተሻና ደረጃ ሲካሄድ ፣ ብዙ ለማምረት በሚደረግ ጥረት የተነሳ የሚፈጠር እና ደረጃውን ያልጠበቀ ተግባር /Lack of standard operation/ ሲደረግ ነው፡፡
ብልሽት(እንከን) ያለው ምርት የማምረት ብክነት(“Muda” of Defect-Making) መንስኤዎች በምርት ሂደት መጨረሻ ላይ ብቃት እና ጥራት ያለው ፍተሻ አለማድረግ፣ በርካታ ምርቶችን ለማምረት በሚደረግ ጥረት ብልሽት ወይም እንከን መፈጠሩ፣ ደረጃውን ያልጠበቀ ተግባር /Lack of standard operation )መከናወኑ እና ሌሎችም ናቸው፡፡
አምራቾች ብልሽት ወይም እንከን ያለው ምርት ሲያመርቱ በገበያው ስለማይፈለግ እንደገና ለማምረት(ማስተካከል)ይገደዳሉ፤ ይህም የድርጅቱ ወጪእንዲንር ያደርጋል፡፡በደንበኞች ዘንድም ቅሬታ ይፈጠራል፡፡
እነዚህም በሰራተኛም ሆነ በማሽን እንቅስቃሴ ላይ እሴት የማይጨምሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ዕቃዎችን መፈለግ፣ ግድፈቶችን መሥራት ወዘተ ናቸው፡፡ ስለሆነም ካምፓኒዎች ብልሽት ወይም እንከን ያለው ምርት የማምረት ብክነት እንዳያጋጥማቸው ብርቱ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡


በማምረት ሂደት ውስጥም ሆነ ተሰርተው ከተጠናቀቁት ውስጥ የጥራት ደረጃቸውን ሳያሟሉ በመቅረታቸው እንደገና መስተካከል ያለባቸው እቃዎች (rejects)፤ቁጥር አነስተኛ ወይም ምንም እንዳይኖር የማድረግ ደረጃ ላይ መድረስ የካይዘን አንዱ አስተምህሮ ነው፡፡

6. የእንቅስቃሴ ብክነት

በማንኛውም ጊዜ፣ቦታና ሁኔታ ስራን ለመስራትም ሆነ ለማምረት እንቅስቃሴ (Motion)ያስፈልጋል፡፡በስራ ቦታ ላይ የሚደረግ አላስፈላጊ ወይም እሴት የማይጨምር (Non value)እንቅስቃሴ የእንቅስቃሴ ብክነት ይባላል፡፡
የእንቅስቃሴ ብክነት(“Muda” of Motion) መንስኤዎች የተለየ ኦፕሬሽን መኖር ፣ትምህርት ወይም ስልጠና አለመኖር፣ደረጃውን ያልጠበቀ የአሠራር ቅደም ተከተል ፣ጥሩ ያልሆነ የማሽኖች አቀማመጥ ፣ትክክለኛ ያልሆነ የባለሙያ አቀማመጥ/አቋቋም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የእንቅስቃሴ ብክነት( “Muda” of Motion) የሚያስከትላቸው በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ፣የሠራተኛን ሙያ መቀነስ ፣የሰው ኃይልና የሥራ ሰዓት መጨመር ፣ያልተረጋጋ ኦፕሬሽን፣አላስፈላጊ እንቅስቃሴ ፣የማምረቻ ጊዜን ማስረዘም ፣የአካል ጉዳት በባለሙያ ላይ ማስከተሉ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

7.የአሠራር ብክነት (“Muda” in Processing)

ይህ የብክነት ዓይነት የማያስፈልጉ ኦፕሬሽኖችን በማከናወን የሚፈጠር ነው፡፡ ተጠቃሚው ከሚፈልገው ደረጃ በላይ አላግባብ የሚያከናውን ሲሆን በስራ ሂደት የሚፈጠሩ ግድፈቶችን ለማስተካከል የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ያጠቃልላል፡፡ ለምሳሌ፡- ችግሮችን ለማጥፋት የሚያስችል ሂደትን በማፍለቅ ፈንታ ሂደቶችን በየጊዜው መፈተሽ
የአሠራር ብክነት (“Muda” in Processing) መንስኤዎች የሂደት ቅድም ተከተሎችን ተንትኖ ያለማወቅ፣የሂደቶችን ይዘት ተንትኖ አለማወቅ ፣ትክክለኛ ያልሆኑ ዕቃዎችና ትክክለኛ ያልሆነ አጠቃቀም፣ ያልተሟላ የደረጃ ወሰን(መደብ)፣አመለካከት፣ ከዚህ ሌላ አሰራር እንደሌለ ማሰብ ናቸው፡፡
ሌሎች ተጨማሪ መንስኤዎች የሚባሉት የማያስፈልግ ሂደት ወይም ኦፕሬሽን ፣የሰው ኃይልን ማብዛትና የሥራ ጊዜን ማራዘም (Lower workability) እና ግድፈቶችን ማብዛት ናቸው፡፡

ብክነቶችን የመለየት ቅደም ተከተል
በስራ ቦታችን ውሰጥ እሴት የማይጨምር ማንኛውም የሰው ልጅ እንቅስቃሴ ብክነት ወይም ሙዳ ነው፡፡ብክነትን የማወቅ አቅማችንን ባሳደግን ቁጥር ብክነቶች ከጅምሩ ሲከሰቱ ለማየት ይረዳናል፡፡ስለሆነም ብክነትን ለማስወገድ ከፍተኛ ትኩረትን፣ ብልሃትን እና ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅ ይታወቃል፡፡

Designed by: HR ICT Solutions PLC  © Ethiopian Kaizen Institute