የካይዘን የማሻሻያ ሥራዎችና ቴክኒኮች

በየትኛውም ደረጃ የሚመሠረቱ የካይዘን ልማት ቡድኖች በቅድሚያ የካይዘንን ዕውቀት በሚገባ መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ የካይዘን ዕውቀት ምሰሶዎች የሚባሉት፤ምርታማነትን ማሻሻል፣ጥራትን ማሻሻል፣ወጪ ቆጣቢ አሰራር፣አቅርቦትን ማፋጠን፣የሥራ ላይ ደህንነትን መጠበቅ፣መነቃቃትና ተነሳሽነት፣አካባቢን መንከባከብ፣የቡድን አሰራር፣ምርጥ ተመክሮ ቅመራ እና አመራር ናቸው፡፡

የካይዘን ቡድኖች በማያሰልስ ሁኔታ በቀጣይነት ጥራትና ምርታማነትን ለማሻሻል ወጪን በመቀነስ ምርታማነትን ለመጨመር፣ አቅርቦትን ለማፋጠን፣ የሥራ ላይ ደህንነትን ለመጠበቅ፣ ተሳትፎን ለማጐልበትና ጥራትን የተላበሰ የሥራ አካባቢን(Quality work environment) ለመፍጠር ዋናው መሣሪያ የማቀድ፣ የመተግበር፣ የማረጋገጥና የማስቀጠል ዑደት ነው፡፡

ማቀድ

የካይዘን ልማት ቡድን አባላት በቅድሚያ የትኛውን ችግር(ማነቆ) መፍታት እንደሚያስፈልግ መወሰን አለባቸው፡፡ ውሣኔው የዓቢይ ልማት ቡድኑን ውሣኔ የሚጠይቅ ከሆነ በዚህ ደረጃ ማስፈቀድ ይኖርባቸዋል፡፡ ዝርዝር የአፈጻጸም መርሀ ግብር ሊዘጋጅም ይገባል፡፡ በማቀድ ደረጃ በዋናነት ሦስት ተግባራት መከናወን ይኖርባቸዋል፡፡

የመጀመሪያው ችግሮችን (ማነቆዎችን) መለየት ነው፡፡ችግሮች(ማነቆዎች) የሚለዩት በቡድኖቹ፣ በአመራሩ ወይም በሠራተኛው ሊሆን ይችላል፡፡ በልማት ቡድኖች ደረጃ የሚተገበሩ የማሻሻያ ሥራዎች ከሥራዎች ጋር የተያያዙ መሆን አለባቸው፡፡የልማት ቡድኖቹ፤ስለ ህብረት ሥራ ስምምነት፣ስለ ስነምግባር ችግር፣ስለግል ጉዳይ፣ስለደመወዝና ጉርሻ(Bonus)፣ስለ በጀት እና ስለ ቅጥር ዝውውርና ዕድገት እንዲሁም በቀጥታ ከሥራ ጋር ባልተያያዙ ችግሮች ላይ እንዲወያዩ አይፈቀድም፡፡ምክንያቱም እነዚህ ችግሮች የሚፈቱበት የአደረጃጀትና የህግ አግባብ ያለው በመሆኑ ነው፡፡

ሁለተኛው ችግሮችን(ማነቆዎችን) በቅደም ተከተል ማስቀመጥ ነው፡፡ባልተገደበ ውይይት (Brain Storming) ቡድኖች በዛ ያሉ ችግሮችን(ማነቆዎችን) ሊለዩ ይችላሉ፡፡ በቅድሚያ ከቀረቡት ችግሮች(ማነቆዎች) መካከል በሥራ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚኖረውን በመለየት በአንድ ጊዜ ወይንም በቅደም ተከተል መፍታት ይሆናል፡፡

ሶስተኛው የትግበራ መርሀግብር ማዘጋጀት ነው፡፡ለተለዩ ችግሮች(ማነቆዎች) የአሠራር ማሻሻያ ማድረግ የሚያስችል ዝርዝር መርሀግብር ይዘጋጃል፡፡ መርሀግብሩ ሲዘጋጅ በዋናነት፤ከካይዘን በፊትና በኋላ ያለውን ሁኔታ ወይም ከትግበራ በኋላ የሚገኘውን ውጤት ማስቀመጥ፣ዝርዝር ተግባራትን መለየት፣ለእያንዳንዱ ዝርዝር ተግባር ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የሚያስፈልገውን ጊዜ መገመት እና የቁጥጥርና ክትትል(ኢንስፔክሽንና ሞኒተሪንግ) ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል::

Designed by: HR ICT Solutions PLC  © Ethiopian Kaizen Institute